Thursday, March 4, 2010

ምዕራፍ 1

1 በብንያም አገር በዓናቶት ከነበሩ ካህናት የሆነ የኬልቅያስ ልጅ የኤርምያስ ቃል።

2 በይሁዳ ንጉሥ በአሞጽ ልጅ በኢዮስያስ ዘመን በመንግሥቱ በአሥራ ሦስተኛው ዓመት የእግዚአብሔር ቃል መጣለት።

3 በይሁዳም ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን፥ እስከ ይሁዳ ንጉሥ እስከ ኢዮስያስ ልጅ እስከ ሴዴቅያስ እስከ አሥራ አንደኛው ዓመት ፍጻሜ፥ ኢየሩሳሌም እስከ ተማረከችበት እስከ አምስተኛው ወር ድረስ መጣ።

4 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።

5 በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ።

6 እኔም። ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም አልሁ።

7 እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ። ወደምሰድድህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፥ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና። ብላቴና ነኝ አትበል።

8 እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና ከፊታቸው አትፍራ፥ ይላል እግዚአብሔር።

9 እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፥ እግዚአብሔርም። እነሆ፥ ቃሌን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፤

10 እነሆ። ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል ዘንድ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ አድርጌሃለሁ አለኝ።

11 ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል። ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም። የለውዝ በትር አያለሁ አልሁ።

12 እግዚአብሔርም። እፈጽመው ዘንድ በቃሌ እተጋለሁና መልካም አይተሃል አለኝ።

13 ሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል። ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም። የሚፈላ አፍላል አያለሁ፥ ፊቱም ከሰሜን ወገን ነው አልሁ።

14 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ከሰሜን ወገን ክፉ ነገር በምድሪቱ በተቀመጡ ሁሉ ላይ ይገለጣል።

15 እነሆ፥ እኔ በሰሜን ያሉትን የመንግሥታትን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እነርሱም ይመጣሉ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም በር መግቢያ በዙሪያዋ በቅጥርዋ ሁሉ ላይ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያስቀምጣሉ።

16 ስለ ክፋታቸውም ሁሉ፥ እኔን ስለ ተው ለሌሎችም አማልክት ስላጠኑ ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ፥ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ።

17 አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፥ ተነሥም፥ ያዘዝሁህም ሁሉ ንገራቸው፤ በፊታቸው እንዳላስፈራህ አትፍራቸው።

18 እነሆ፥ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በይሁዳም ነገሥታት በአለቆችዋና በካህናትዋ ላይ በምድሪቱም ሕዝብ ላይ እንደ ተመሸገ ከተማ እንደ ብረትም ዓምድ እንደ ናስም ቅጥር ዛሬ አድርጌሃለሁ።

19 ከአንተ ጋር ይዋጋሉ፥ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም፥ ይላል እግዚአብሔር።

ምዕራፍ 2

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።

2 ሂድ፥ በኢየሩሳሌም ጆሮ ጩኽ፥ እንዲህም በል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የብላቴንነትሽን ምሕረት የታጨሽበትንም ፍቅር፥ በምድረ በዳ ዘር ባልተዘራበት ምድር እንደ ተከተልሽኝ አስቤአለሁ።

3 እስራኤል ለእግዚአብሔር ቅዱስ ነበረ፥ የቡቃያውም በkWraት ነበረ፤ የበሉት እንደ በደለኞች ይቈጠራሉ፥ ክፉም ነገር ያገኛቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር።

4 የያዕቆብ ቤት የእስራኤልም ቤት ወገኖች ሁሉ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አባቶቻችሁ ከእኔ ዘንድ የራቁ፥ ከንቱነትንም የተከተሉ፥ ከንቱም የሆኑ ምን ክፋት አግኝተውብኝ ነው?

6 እነርሱም። ከግብጽ ምድር ያወጣን፥ በምድረ በዳም በባድማ gWdጓድም ባለበት ምድር፥ በውኃ ጥምና በሞት ጥላ ምድር፥ ማንም በማያልፍበትና ማንም በማይቀመጥበት ምድር የመራን እግዚአብሔር ወዴት አለ? አላሉም።

7 ፍሬዋንና በረከትዋንም ትበሉ ዘንድ ወደ ፍሬያማ ምድር አገባኋችሁ፤ ነገር ግን በገባችሁ ጊዜ ምድሬን አረከሳችሁ፥ ርስቴንም አጐሳቈላችሁ።

8 ካህናቱም። እግዚአብሔር ወዴት አለ? አላሉም፥ ባለ ኦሪቶችም አላወቁኝም፤ ገዢዎችም ዐመፁብኝ፥ ነቢያትም በበኣል ትንቢት ተናገሩ፥ የማይረባንም ነገር ተከተሉ።

9 ስለዚህ ከእናንተ ጋር እከራከራለሁ፥ ከልጆቻችሁም ልጆች ጋር እከራከራለሁ።

10 ወደ ኪቲም ደሴቶች እለፉና ተመልከቱ፥ ወደ ቄዳርም ላኩና እጅግ መርምሩ፥ እንደዚህም ያለ ነገር ህኖ እንደ ሆነ እዩ።

11 በውኑ አማልክት ያልሆኑትን አማልክቱን የለወጣቸው አንድ ሕዝብ አለን? ነገር ግን ሕዝቤ ክብሩን ለማይረባ ነገር ለወጠ።

12 ሰማያት ሆይ፥ በዚህ ተደነቁ፥ እጅግም ደንግጡና ተንጥቀጡ ይላል እግዚአብሔር።

13 ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና፤ እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል፥ የተቀደዱትንም gWdጓዶች፥ ውኃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን gWdጓዶች፥ ለራሳቸው ቆፍረዋል።

14 በውኑ እስራኤል ባሪያ ነውን? ወይስ የቤት ውላጅ ነውን? ስለምን ብዝበዛ ሆነ?

15 የአንበሳ ደቦሎች በእርሱ ላይ አገሡ፥ ድምፃቸውንም ሰጡ፤ ምድሩንም ባድማ አደረጉ፥ ከተሞቹም ተቃጠሉ የሚቀመጥባቸውም የለም።

16 የሜምፎስና የጣፍናስ ልጆች አስነወሩሽ አላገጡብሽም።

17 ይህ ሁሉ የሆነብሽ እኔን ስለ ተውሽ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር አምላክሽ።

18 አሁንስ የሺሖርን ውኃ ትጠጪ ዘንድ በግብጽ መንገድ ምን ጉዳይ አለሽ? የኤፍራጥስንም ውኃ ትጠጪ ዘንድ በአሦር መንገድ ምን ጉዳይ አለሽ?

19 ክፋትሽ ይገሥጽሻል ክዳትሽም ይዘልፍሻል፤ አምላክሽንም እግዚአብሔርን የተውሽ እኔንም መፍራት የሌለብሽ ክፉና መራራ ነገር እንደ ሆነ እወቂ፥ ተመልከቺ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

20 ከጥንት ጀምሮ ቀንበርሽን ሰብሬአለሁ እስራትሽንም ቈርጫለሁ፤ አንቺም። አላገለግልም አልሽ፥ ነገር ግን ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ ከለምለምም ዛፍ ሁሉ በታች ለማመንዘር ተጋደምሽ።

21 እኔ የተመረጠች ወይን ፍጹምም እውነተኛ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤ አንቺ ግን ክፉ የእንግዳ ወይን ግንድ ሆነሽ እንዴት ተለወጥሽብኝ?

22 በእንዶድ ብትታጠቢም፥ ለራስሽም ሳሙና ብታበዢ፥ በእኔ ፊት በኃጢአትሽ ረክሰሻል ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

23 አንቺስ። አልረከስሁም በአሊምንም አልተከተልሁም እንዴት ትያለሽ? በቈላ ያለውን መንገድሽን ተመልከቺ፥ ያደረግሽውንም እወቂ፤ በመንገድም ላይ እንደ ተለቀቀች እንደ ፈጣን ግመል ሆነሻል፤

24 በምኞትዋ ነፋስን እንደምታሸትት፥ በምድረ በዳ እንደ ለመደች እንደ ሜዳ አህያ ነሽ፤ ከምኞትዋ የሚመልሳት ማን ነው? የሚሹአት ሁሉ አይደክሙም፥ በወራትዋ ያገኙአታል።

25 እግርሽን ከሸካራ መንገድ gWroሮሽንም ከውኃ ጥም ከልክዪ፤ አንቺ ግን። እጨክናለሁ፥ እንግዶችን ወድጄአለሁና፥ እከተላቸዋለሁም አልሽ።

26 ሌባ በተያዘ ጊዜ እንደሚያፍር እንዲሁ የእስራኤል ቤት፥ እነርሱና ንጉሦቻቸውም አለቆቻቸውም ካህናቶቻቸውም ነቢያቶቻቸውም ያፍራሉ።

27 ግንዱን።አንተ አባቴ ነህ፤ ድንጋዮንም። አንተ ወለድኸኝ ይላሉ፤ ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ፥ በመከራቸው ጊዜ ግን። ተነሥተህ አድነን ይላሉ።

28 ለአንተ የሠራሃቸው አማልክትህ ወዴት ናቸው? ይሁዳ ሆይ፥ አማልክትህ እንደ ከተሞችህ KWTር እንዲሁ ናቸውና ይነሡ በመከራህም ጊዜ ያድኑህ።

29 ከእኔ ጋር የምትከራከሩ ለምንድር ነው? ሁላችሁ ዐምፃችሁብኛል ይላል እግዚአብሔር።

30 ልጆቻችሁን በከንቱ ቀሥፌአቸዋለሁ፤ ተግሣጽን አልተቀበሉም፤ ሰይፋችሁ እንደሚሰብር አንበሳ ነቢያቶቻችሁን በልቶአል።

31 ትውልድ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ተመልከቱ። በውኑ ለእስራኤል ምድረ በዳ ወይስ የጨለመች ምድር ሆንሁባትን? ሕዝቤስ ስለ ምን። እኛ ፈርጥጠናል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንተ አንመለስም ይላል?

32 በውኑ ቆንጆ ጌጥዋን ወይስ ሙሽራ ዝርግፍ ጌጥዋን ትረሳለችን? ሕዝቤ ግን የማይቈጠር ወራት ረስቶኛል።

33 ፍቅርን ለመሻት መንገድሽን እንዴት ታቀኛለሽ! ስለዚህ ለክፉዎች ሴቶች እንኳ መንገድሽን አስተምረሻል።

34 በእጆችሽም የንጹሐን ድሆች ደም ተገኝቶአል፤ በእነዚህ ሁሉ ላይ በግልጥ አገኘሁት እንጂ በስውር ፈልጌ አላገኘሁትም።

35 አንቺ ግን። ንጹሕ ነኝ፤ በእውነት KWTaው ከእኔ ተመልሶአል አልሽ። እነሆ። ኃጢአት አልሠራሁም ብለሻልና በፍርድ እከስስሻለሁ።

36 መንገድሽን ትለውጪ ዘንድ ለምን እጅግ ትሮጫለሽ? አሦር እንዳሳፈረሽ ግብጽ ያሳፍርሻል።

37 እግዚአብሄር የታመንሽባቸውን ጥሎአልና፥ በእነርሱም አይከናወንልሽምና እጅሽን በራስሽ ላይ አድርገሽ ከዚያ ደግሞ ትወጫለሽ። a

ምዕራፍ 3

1 በሰው ዘንድ። ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ዘንድ ሄዳ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ በውኑ ደግሞ ወደ እርሱ ትመለሳለችን? ያች ሴት እጅግ የረከሰች አይደለችምን? ይባላል። አንቺ ከብዙ ውሽሞች ጋር አመንዝረሻል፥ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል እግዚአብሔር።

2 ዓይንሽን አንሥተሽ ወደ ወናዎች ኮረብቶች ተመልከቺ፤ ያልተጋደምሽበት ስፍራ ወዴት አለ? ዓረባዊ በምድረ በዳ እንደሚቀመጥ አንቺ በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ ትጠብቂያቸው ነበር፤ በግልሙትናሽና በኃጢአትሽ ምድሪቱን አረከስሽ።

3 ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፥ የኋለኛውም ዝናብ ጠፋ፤ የጋለሞታም ሴት ፊት ነበረብሽ፥ ታፍሪም ዘንድ እንቢ ብለሻል።

4 አሁንም። አንተ አባቴ ሆይ፥ የብላቴንነቴ ወዳጅ ነህ ብለሽ አልጮኽሽልኝምን? ለዘላለም ይቈጣልን?

5 እስከ ፍጻሜስ ድረስ ይጠብቀዋልን? እነሆ፥ እንዲህ ብለሽ ተናገርሽ፥ እንደ ተቻለሽም መጠን ክፉን ነገር አደረግሽ።

6 እግዚአብሔርም በንጉሡ በኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ። ከዳተኛይቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ወደ ረዘመው ተራራ ሁሉ ከለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች በዚያም ጋለሞተች።

7 ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ። ወደ እኔ ትመለሳለች ብዬ ነበር፤ ነገር ግን አልተመለሰችም፤ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች።

8 ከዳተኛይቱም እስራኤል ስላመነዘረች ስለዚህ ፈትቻታለሁ የፍችዋንም ወረቀት ሰጥቻታለሁ፤ አታላይ እኅትዋ ይሁዳ ግን እንዳልፈራች እርስዋም ደግሞ ሄዳ እንደ ጋለሞተች አየሁ።

9 በግልሙትናዋም በመቅለልዋም ምድሪቱ ረከሰች፤ እርስዋም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች።

10 በዚህም ሁሉ አታላይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም።

11 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ከአታላይቱ ከይሁዳ ይልቅ ከዳተኛይቱ እስራኤል ጸደቀች።

12 ሂድና ይህን ቃል ወደ ሰሜን ተናገር፥ እንዲህም በል። ከዳተናይቱ እስራኤል ሆይ፥ ተመለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ መሐሪ ነኝና፥ ለዘላለምም አልቈጣምና በእናንተ ላይ ፊቴን አላደርግም፥ ይላል እግዚአብሔር።

13 በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ቃሌንም እንዳልሰማሽ ኃጢአትሽን ብቻ እወቂ ይላል እግዚአብሔር።

14 ከዳተኞች ልጆች ሆይ፥ እኔ ባላችሁ ነኝና ተመለሱ ይላል እግዚአብሔር፤ አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፥ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፤

15 እንደ ልቤም በግ ጠባቆችን እሰጣችኋለሁ፥ በእውቀትና በማስተዋልም ይጠብቁአችኋል።

16 በበዛችሁም ጊዜ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ዘመን። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፤ ልብ አያደርጉትም፥ አያስቡትምም፥ አይሹትምም፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም።

17 በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን የእግዚአብሔር ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርስዋ ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልከኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም።

18 በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳል፤ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ።

19 እኔ ግን። ከወንዶች ልጆች ጋር እንዴት አደርግሻለሁ? ያማረችውንስ ምድር የከበረችውን የአሕዛብን ሠራዊት ርስት እንዴት እሰጥሻለሁ? ብዬ ነበር። ደግሞ። አባቴ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እኔንም ከመከተል አትመለሽም ብዬ ነበር።

20 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ሚስት ባልዋን እንደምታታታልል እንዲሁ አታለላችሁኝ ይላል እግዚአብሔር።

21 የእስራኤል ልጆች መንገዳቸውን አጣምመዋልና፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተዋልና በወናዎች ኮረብቶች ላይ የልመናቸውና ልቅሶአቸው ድምፅ ተሰማ።

22 ከዳተኞች ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከዳተኛነታችሁንም እፈውሳለሁ። እነሆ፥ አንተ አምላካችን እግዚአብሔር ነህና ወደ አንተ እንመጣለን።

23 በእውነት የኮረብቶችና የተራሮች ፍጅት ከንቱ ናት፤ በእውነት የእስራኤል መዳን በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

24 ነገር ግን ከትንሽነታችን ጀምሮ የአባቶቻችን ድካም፥ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም፥ እፍረት በልቶባቸዋል።

25 ከትንሽነታችን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኛና አባቶቻችን በአምላካችን በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርተናልና፥ የአምላካችንንም የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማንምና በእፍረታችን እንጋደም፥ ውርደታችንም ይክደነን።

ምዕራፍ 4

1 እስራኤል ሆይ፥ ብትመለስ፥ ወደ እኔ ተመለስ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ርkWsvትህንም ከፊቴ ብታስወግድ፥ ባትናወጥም፥

2 ሕያው እግዚአብሔርን! ብለህም በእውነትና በቅንነት በጽድቅም ብትምል፥ አሕዛብ በእርሱ ይባረካሉ በእርሱም ይመካሉ።

3 እግዚአብሔር ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሰዎች እንዲህ ይላልና። ጥጋቱን እርሻ እረሱ በእሾህም ላይ አትዝሩ።

4 እናንተም የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሆይ፥ ስለ ሥራችሁ ክፋት KWTaዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳያቃጥል፥ ለእግዚአብሔር ተገረዙ፥ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ።

5 በይሁዳ ዘንድ ተናገሩ በኢየሩሳሌምም ላይ አውሩና። በአገሪቱ ላይ መለከት ንፉ በሉ፤ ጮኻችሁም። ሁላችሁ ተሰብሰቡ ወደ ተመሸጉትም ከተሞች እንግባ በሉ።

6 ከሰሜን ክፉ ነገርንና ጽኑ ጥፋትን አመጣለሁና ወደ ጽዮን ዓላማን አንሡ፤ ሽሹ፥ አትዘግዩ።

7 አንበሳ ከጭፍቅ ዱር ወጥቶአል፥ አሕዛብንም የሚዘርፍ ተነሥቶአል፤ ምድርሽን ባድማ ያደርግ ዘንድ ከስፍራው ወጥቶአል፥ ከተሞችሽም ሰው የሌለባቸው ፍርስራሾች ይሆናሉ።

8 የእግዚአብሔር ጽኑ KWTa ከእኛ ዘንድ አልተመለሰምና ማቅ ልበሱ፥ አልቅሱም ዋይም በሉ።

9 በዚያም ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የንጉሡና የመኳንንቱ ልብ ይጠፋል፥ ካህናቱም ይደነቃሉ ነቢያቱም ይደነግጣሉ።

10 እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ፥ አንተ ሰይፍ እስከ ነፍስ ድረስ በደረሰ ጊዜ። ሰላም ይሆንላችኋል ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን እጅግ አታለልህ አልሁ።

11 በዚያ ጊዜ ለዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም። ለማበጠር ወይም ለማጥራት ሳይሆን የሚያቃጥል ነፋስ በምድረ በዳ ካሉ ከወናዎች ኮረብቶች ወደ ወገኔ ሴት ልጅ ይመጣል፤

12 ስለ እኔ ጽኑ የሆነ ነፋስ ከእነዚህ ይመጣል ይባላል። አሁንም እኔ ደግሞ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ።

13 እነሆ፥ እንደ ደመና ይወጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ፤ ፈረሶቹም ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው። ጠፍተናልና ወዮልን።

14 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ትድኚ ዘንድ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ። ክፉ አሳብ የሚኖርብሽ እስከ መቼ ድረስ ነው?

15 የተናጋሪ ድምፅ ከዳን ዘንድ ይናገራልና፥ ከኤፍሬምም ኮረብቶች መከራን ያወራልና።

16 ለአሕዛብ አሰሙና። እነሆ፥ ጠባቂዎች ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤ በይሁዳም ከተሞች ላይ ይጮኻሉ ብላችሁ በኢየሩሳሌም ላይ አውሩ።

17 በእኔ ላይ ዓመፀኛ ሆናለችና በዙሪያዋ ከብበው እንደ እርሻ ጠባቂዎች ሆነውባታል፥ ይላል እግዚአብሔር።

18 መንገድሽና ሥራሽ ይህን አድርጎብሻል፤ ይህ ክፋትሽ መራር ነው፥ ወደ ልብሽም ደርሶአል።

19 አንጀቴ! አንጀቴ! ልቤ በጣም ታምሞአል፥ በውስጤም ልቤ ታውኮብኛል፤ ነፍሴ ሆይ፥ የመለከትን ድምፅና የሰልፍን ውካታ ሰምተሻልና ዝም እል ዘንድ አልችልም።

20 መከራ በመከራ ላይ ተጠርቶአል፤ ምድርም ሁሉ ተበዝብዛለችና፤ በድንገትም ድንኳኔ በቅጽበት ዓይንም መጋረጃዎቼ ጠፉ።

21 ዓላማውን የምመለከት፥ የመለከቱንስ ድምፅ የምሰማ እስከ መቼ ነው?

22 ሕዝቤ ሰንፈዋልና አላወቁኝም፤ ሰነፎች ልጆች ናቸው፥ ማስተዋልም የላቸውም፤ ክፉ ነገርን ለማድረግ ብልሃተኞች ናቸው፥ በጎ ነገርን ማድረግ ግን አያውቁም።

23 ምድሪቱን አየሁ፥ እነሆም፥ ባዶ ነበረች አንዳችም አልነበረባትም፤ ሰማያትንም አየሁ፥ ብርሃንም አልነበረባቸውም።

24 ተራሮችን አየሁ፥ እነሆም፥ ተንቀጠቀጡ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ተናወጡ።

25 አየሁ፥ እነሆም፥ ሰው አልነበረም፥ የሰማይም ወፎች ሁሉ ሸሽተው ነበር።

26 አየሁ፥ እነሆም፥ ፍሬያማ እርሻ ምድረ በዳ ሆነች፥ ከተሞችም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፊት ከጽኑ KWTaው የተነሣ ፈርሰው ነበር።

27 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ምድር ሁሉ ባድማ ትሆናለች፥ ነገር ግን ፈጽሜ አላጠፋትም።

28 ስለዚህ ምድር ታለቅሳለች፥ በላይም ሰማይ ይጠKWraል፤ ተናግሬአለሁና፥ አስቤአለሁም፤ አልጸጸትም ከእርሱም አልመለስም።

29 ከፈረሰኞችና ከቀስተኞች ድምፅ የተነሣ ከተማ ሁሉ ሸሽታለች፤ ወደ ችፍግ ዱርም ይገባሉ በቋጥኝ ላይም ይወጣሉ፤ ከተማ ሁሉ ተለቅቃለች የሚቀመጥባትም ሰው የለም።

30 አንቺም የተበዘበዝሽ ሆይ፥ ምን ታደርጊአለሽ? ቀይ በለበስሽ ጊዜ፥ በወርቅ አንባርም ባጌጥሽ ጊዜ፥ ዓይንሽንም በkWl በተኳልሽ ጊዜ፥ በከንቱ ታጌጫለሽ፤ ውሽሞችሽ አቃለሉሽ፥ ነፍስሽን ይሹአታል።

31 እንደምታምጥ የበkWrዋንም እንደምትወልድ ሴት ድምፅ ሰምቻለሁና፤ የጽዮን ሴት ልጅ ድምፅ በድካም ይሰልላል፥ እጆችዋንም ትዘረጋለችና። ተገድለው ከሞቱት የተነሣ ነፍሴ ዝላለችና ወዮልኝ! አለች።

ምዕራፍ 5

1 በኢየሩሳሌም መንገድ እየተመላለሳችሁ ሩጡ፥ ተመልከቱም፥ እወቁም፥ በአደባባይዋም ፈልጉ፤ ፍርድን የሚያደርገውን እውነትንም የሚሻውን ሰው ታገኙ እንደሆነ ይቅር እላታለሁ።

2 እነርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! ቢሉ የሚምሉት በሐሰት ነው።

3 አቤቱ፥ ዓይንህ እውነትን የምትመለከት አይደለችምን? አንተ ቀሥፈሃቸዋል ነገር ግን አላዘኑም፥ ቀጥቅጠሃቸውማል ነገር ግን ተግሣጽን እንቢ አሉ፤ ፊታቸውን ከድንጋይ ይልቅ አጠንክረዋል፤ ይመለሱ ዘንድ እንቢ አሉ።

4 እኔም። የእግዚአብሔርን መንገድና የአምላካቸውን ሕግ አላወቁምና እነዚህ በእውነት ድሆችና ሰነፎች ናቸው፤

5 ወደ ታላላቆቹ እሄዳለሁ እናገራቸውማለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንገንድና የአምላካቸውን ሕግ ያውቃሉና አልሁ። እነዚህ ግን ቀንበሩን በአንድነት ሰብረዋል፥ እስራቱንም ቈርጠዋል።

6 ስለዚህ ኃጢአታቸው በዝቶአልና፥ የክዳታቸውም ብዛት ጸንቶአልና ስለዚህ አንበሳ ከዱር ወጥቶ ይሰብራቸዋል፥ የበረሀም ተkWla ያጠፋቸዋል፥ ነብርም በከተሞቻቸው ላይ ይተጋል፥ ከዚያም የሚወጣ ሁሉ ይነጠቃል።

7 በእነዚህ ነገሮች ይቅር የምልሽ እንዴት አድርጌ ነው? ልጆችሽ ትተውኛል አማልክትም ባልሆኑ ምለዋል፤ ካጠገብኋቸውም በኋላ አመነዘሩ በጋለሞቶቹም ቤት ተሰበሰቡ።

8 እንደ ተቀለቡ ፈረሶች ሆኑ፤ እያንዳንዳቸውም ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ኋላ አሽካኩ።

9 በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን?

10 ወደ ቅጥርዋ ወጥታችሁ አፍርሱ፥ ነገር ግን ፈጽማችሁ አታጥፉ፤ ለእግዚአብሔር አይደሉምና ቅርንጫፍዋን ውሰዱ።

11የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት በእኔ ላይ እጅግ ወንጅለዋል ይላል እግዚአብሔር።

12 እነርሱም። እርሱ አይደለም፥ ክፉ ነገርም አይመጣብንም ሰይፍንና ራብንም አናይም፤ ነቢያትም ነፋስ ይሆናሉ፥

13 የእግዚአብሔርም ቃል በእነርሱ ዘንድ የለም፥ እንዲህም ይደረግባቸዋል ብለው እግዚአብሔርን ክደዋል።

14 ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህ ቃል ተናግራችኋልና እነሆ፥ በአፍህ ውስጥ ቃሌን እሳት ይህንም ሕዝብ እንጨት አደርጋለሁ፥ ትበላቸውማለች።

15 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እነሆ፥ ሕዝብን ከሩቅ አመጣባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃያል ጥንታዊ ሕዝብ ነው፥ ቋንቋቸውንም የማታውቀው የሚናገሩትንም የማታስተውለው ሕዝብ ነው።

16 የፍላጻቸውም ሰገባ እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ ሁሉም ኃያላን ናቸው።

17 መከርህንና እንጀራህን ይበላሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህንም ይበሉአቸዋል፤ በጎችህንና ላሞችህንም ይበላሉ፤ ወይንህንና በለስህንም ይበላሉ፤ የምትታመናቸውን የተመሸጉ ከተሞችን በሰይፍ ይደበድባሉ።

18 ነገር ግን በዚያ ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ፈጽሜ አላጠፋችሁም።

19 እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ። አምላካችን እግዚአብሔር ይህን ነገር ሁሉ ስለምን አደረገብን? ብትሉ፥ አንተ። እንደ ተዋችሁኝ በአገራችሁም ሌሎችን አማልክት እንዳመለካችሁ፥ እንዲሁ ለእናንተ ባልሆነ አገር ለሌሎች ሰዎች ትገዛላችሁ ትላቸዋለህ።

20 ይህን በያዕቆብ ቤት አውሩ፥ በይሁዳም አሰሙ።

21 እናንተ ሰነፎች ልበ ቢሶች፥ ዓይን እያላችሁ የማታዩ፥ ጆሮም እያላችሁ የማትሰሙ ሕዝብ ሆይ፥ ይህን ስሙ።

22 በውኑ እኔን አትፈሩምን? ከፊቴስ አትደነግጡምን? ይላል እግዚአብሔር፤ እንዳያልፍ አሸዋን በዘላለም ትእዛዝ ለባሕር ዳርቻ አድርጌአለሁ፤ ሞገዱም ቢናወጥ አያሸንፍም፥ ቢጮኽም አያልፍበትም።

23 ለዚህ ሕዝብ ግን የሸፈተና ያመፀ ልብ አላቸው፤ ዐምፀዋል ሄደውማል።

24 በልባቸውም። የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በጊዜው የሚሰጠውን፥ ለመከርም የተመደቡትን ወራት የሚጠብቅልንን አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፍራ አላሉም።

25 በደላችሁ እነዚህን አስቀርታለች፥ ኃጢአታችሁም መልካምን ነገር ከለከለቻችሁ።

26 በሕዝቤ መካከል ክፉዎች ሰዎች ተገኝተዋል፤ እንደ አጥማጆችም ያደባሉ፥ ወጥመድንም ይዘረጋሉ ሰዎችንም ያጠምዳሉ።

27 ቀፎ ወፎችን እንደሚሞላ፥ እንዲሁ ቤታቸው ሽንገላን ሞልታለች፤እንዲሁም ከብረዋል ባለ ጠጎችም ሆነዋል።

28 ወፍረዋል ሰብተውማል፥ ክፋታቸውንም ያለ ልክ አብዝተዋል፤ የድሀ አደጎች ነገር መልካም እንዲሆን አልተምዋገቱላቸውም፥ የችግረኞችንም ፍርድ አልፈረዱላቸውም።

29 በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን?

30 የምታስደንቅና የምታስደነግጥ ነገር በምድር ላይ ሆናለች፤

31 ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፥ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ፤ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ?

ምዕራፍ 6

1 እናንተ የብንያም ልጆች፥ ክፉ ነገር ታላቅም ጥፋት ከሰሜን ይጐበኛልና ከኢየሩሳሌም ውስጥ ሽሹ፥ በቴቁሔ መለከቱን ንፉ፥ በቤትሐካሪም ላይ ምልክት አንሡ።

2 የተዋበችውንና የተሰባቀለችውን የጽዮንን ልጅ አጐሰቍላለሁ።

3 እረኞችና መንጐቻቸው ወደ እርስዋ ይመጣሉ፥ በዙሪያዋም ድንኳኖቻቸውን ይተክሉባታል፥ እያንዳንዱም በስፍራው መንጋውን ያሰማራል።

4 በእርስዋ ላይ ሰልፍ አዘጋጁ ተነሡ፥ በቀትርም እንውጣ። ቀኑ መሽቶአልና፥ የማታውም ጥላ ረዝሞአልና ወዮልን።

5 ተነሡ በሌሊትም እንውጣ፥ አዳራሾችዋንም እናፍርስ።

6 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ዛፎችዋን ቍረጡ፥ በኢየሩሳሌምም ላይ አፈርን ደልድሉ፤ ይህች ከተማ የምትቀሠፍ ናት፤ መካከልዋ ሁሉ ግፍ ብቻ ነው።

7 በጕድጓድ ውኃ እንደሚፈልቅ፥ እንዲሁ ክፋትዋ ከእርስዋ ዘንድ ይፈልቃል፤ ግፍና ቅሚያ በእርስዋ ዘንድ ይሰማል፥ ደዌና ቍስልም ሁልጊዜ በፊቴ አለ።

8 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነፍሴ ከአንቺ እንዳትለይ፥ አንቺንም ባድማና ወና እንዳላደርግሽ፥ ተግሣጽን ተቀበዪ።

9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰው ወይኑን እንደሚቃርም፥ እንዲሁ ከእስራኤል የቀሩትን ፈጽሞ ይቃርሙአቸዋል፤ እጅህንም እንደ ለቃሚ ወደ እንቅብ ዘርጋ።

10 ይሰሙኝስ ዘንድ ለማን እናገራለሁ? ለማንስ አስጠነቅቃለሁ? እነሆ፥ ጆሮአቸው ያልተገረዘች ናት ለመስማትም አይችሉም፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቃል ለስድብ ሆኖባቸዋል፥ ደስም አያሰኛቸውም።

11 ስለዚህ በእግዚአብሔር ቍጣ ተሞልቻለሁ፤ ከመታገሥ ደክሜአለሁ፤ በሜዳ በሕፃናት ላይ በጕልማሶችም ጉባዔ ላይ በአንድነት አፍስሰው፤ ባል ከሚስቱ ጋር ሽማግሌውም ከጎበዙ ጋር ይያያዛልና።

12 እጄን በምድር በሚኖሩ ላይ እዘረጋለሁና ቤቶቻቸው እርሻዎቻቸውም ሴቶቻቸውም በአንድነት ለሌሎች ይሆናሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።

13 ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ስስትን ያስባሉና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ በተንኰል ያደርጋሉና።

14 የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን። ሰላም ሰላም ይላሉ።

15 ርኩስን ነገር ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።

16 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን። አንሄድባትም አሉ።

17 እኔም። የመለከቱን ድምፅ አድምጡ ብዬ ጠባቆችን ሾምሁባችሁ፤ እነርሱ ግን። አናደምጥም አሉ።

18 አሕዛብ ሆይ፥ ስለዚህ ስሙ፤ ማኅበር ሆይ፥ እነዚያ የሚያገኛቸውን እወቁ።

19 ምድር ሆይ፥ ስሚ፤ እነሆ፥ ቃሌን ስላልሰሙ ሕጌንም ስለ ጣሉ በዚህ ሕዝብ ላይ የአሳባቸውን ፍሬ ክፉን ነገር አመጣባቸዋለሁ።

20 ስለ ምንስ ከሳባ ዕጣንን፥ ከሩቅም አገር ቀረፋን ታቀርቡልኛላችሁ? የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን አልቀበለውም ሌላ መሥዋዕታችሁም ደስ አያሰኘኝም።

21 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ከዚህ ሕዝብ ፊት ዕንቅፋቶችን አደርጋለሁ፤ አባቶችና ልጆች በአንድነት ይሰናከሉባቸዋል፥ ጎረቤትና ባልንጀራም ይጠፋሉ።

22 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሕዝብ ከሰሜን አገር ይመጣል፥ ታላቅ ሕዝብም ከምድር ዳርቻ ይነሣል።

23 ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፤ ጨካኞች ናቸው፥ ምሕረትንም አያደርጉም፤ ድምፃቸው እንደ ባሕር ይተምማል፥ በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፤ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፥ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ።

24 ወሬውን ሰምተናል፥ እጃችን ደክማለች፤ ምጥ ወላድን ሴት እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞናል።

25 የጠላት ሰይፍና ድንጋጤ ከብበዋችኋልና ወደ ሜዳ አትውጡ በምንገድም ላይ አትሂዱ።

26 የሕዝቤ ልጅ ሆይ፥ ማቅ ልበሺ በአመድም ውስጥ ተንከባለዪ፤ አጥፊ በላያችን በድንገት ይመጣብናልና ለአንድያ ልጅ እንደሚደረግ ልቅሶ፥ መራራ ልቅሶ አልቅሺ።

27 መንገዳቸውን እንድታውቅና እንድትፈትን በሕዝቤ መካከል ፈታኝ አድርጌሃለሁ።

28 እነርሱ ሁሉ እጅግ ዓመፀኞች ናቸው፤ በጠማማነት ይሄዳሉ፤ ናስና ብረት ናቸው፤ ሁሉ ርኵሰትን ያደርጋሉ።

29 ወናፍ አናፋ እርሳሱም በእሳት ቀለጠ፤ አንጥረኛውም መልሶ በከንቱ ያቀልጠዋል፤ ኃጢአተኞች አልተወገዱም።

30 እግዚአብሔር ጥሎአቸዋልና የተጣለ ብር ብለው ይጠሩአቸዋል።

ምዕራፍ 7

1 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው።

2 በእግዚአብሔር ቤት በር ቁም፥ ይህንም ቃል እንዲህ ብለህ ተናገር። እግዚአብሔርን ልታመልኩ በእነዚህ በሮች የምትገቡ ከይሁዳ ያላችሁ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

3 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ በዚህም ስፍራ አሳድራችኋለሁ።

4 የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ ይህ ነው እያላችሁ በሐሰት ቃል አትታመኑ።

5 መንገዳችሁንና ሥራችሁን ፈጽማችሁ ብታሳምሩ፥ በሰውና በጎረቤቱ መካከል ቅን ፍርድ ብትፈርዱ፥

6 መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም ባትገፉ፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን ባታፈስሱ፥ ክፉም ሊሆንባችሁ እንግዶችን አማልክት ባትከተሉ፥

7 ከዘላለም እስከ ዘላለም ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር በዚህ ስፍራ አሳድራችኋለሁ።

8 እነሆ፥ በማትረቡበት በሐሰት ቃል ታምናችኋል።

9 ትሰርቃላችሁ፥ ትገድላላችሁ፥ ታመነዝራላችሁ፥ በሐሰትም ትምላላችሁ፥ ለበኣልም ታጥናላችሁ፥ የማታውቋቸውንም እንግዶች አማልክት ትከተላላችሁ፤

10 መጣችሁም፥ ስሜም በተጠራበት በዚህ ቤት በፊቴ ቆማችሁ። ይህን አስጸያፊ የሆነ ነገርን ሁሉ አላደረግንም አላችሁ።

11 ይህስ ስሜ የተጠራበት ቤት በዓይናችሁ የሌቦች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፥ እኔ አይቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

12 ነገር ግን በቀድሞ ዘመን ስሜን ወዳሳደርሁበት በሴሎ ወደ ነበረው ስፍራዬ ሂዱ፥ ከሕዝቤም ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ያደረግሁበትን እዩ።

13 አሁንም ይህን ነገር ሁሉ ስላደረጋችሁ፥ በማለዳም ተነሥቼ በተናገርኋችሁ ጊዜ ስላልሰማችሁ፥ በጠራኋችሁም ጊዜ ስላልመለሳችሁ፥

14 ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ እንዲሁ ስሜ በተጠራበት በምትታመኑበት ቤት ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ስፍራ አደርጋለሁ።

15 የኤፍሬምንም ዘር ሁሉ፥ ወንድሞቻችሁን ሁሉ እንደ ጣልሁ፥ እንዲሁ ከፊቴ እጥላችኋለሁ።

16 እንግዲህም አልሰማህምና ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ፤ አትማልድላቸው።

17 እነርሱስ በይሁዳ ከተሞች ውስጥና በኢየሩሳሌም አደባባይ ላይ የሚያደርጉትን አታይምን?

18 ያስቈጡኝ ዘንድ፥ ለሰማይ ንግሥት እንጐቻ እንዲያደርጉ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን እንዲያፈስሱ ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ፥ አባቶችም እሳት ያነድዳሉ፥ ሴቶችም ዱቄት ይለውሳሉ።

19 እኔን ያስቈጣሉን? ይላል እግዚአብሔር፤ ለፊታቸውስ እፍረት አይደለምን?

20 እንግዲህም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ ላይ፥ በሰውና በእንስሳ ላይ፥ በዱር ዛፎችና በምድር ፍሬ ላይ ይፈስሳል፤ ይነድዳል፥ አይጠፋምም።

21 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለሌላ መሥዋዕታችሁ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን ጨምሩ፥ ሥጋውንም ብሉ።

22 ከግብጽ ምድር ባወጣኋችሁ ቀን ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሌላ መሥዋዕት ለአባቶቻችሁ አልተናገርሁምና፥ አላዘዝኋቸውምም።

23 ነገር ግን። ቃሌን ስሙ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ መልካምም ይሆንላችሁ ዘንድ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ በዚህ ነገር አዘዝኋቸው።

24 ነገር ግን በክፉ ልባቸው አሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደ ፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም።

25 አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር።

26 ነገር ግን አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ አባቶቻቸውም ካደረጉት ይልቅ የባሰ አደረጉ።

27 በዚህም ቃል ሁሉ ትነግራቸዋለህ፥ ነገር ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸውማለህ፥ ነገር ግን አይመልሱልህም።

28 አንተም። የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቃል ያልሰማ፥ ተግሣጽንም ያልተቀበለ ሕዝብ ይህ ነው፤ እውነት ጠፍቶአል ከአፋቸውም ተቈርጦአል ትላቸዋለህ።

29 እግዚአብሔር የቍጣውን ትውልድ ጥሎአልና፥ ትቶታልምና ጠጕርሽን ቍረጪ፥ ጣዪውም፥ በወናዎች ኮረብቶችም ላይ አሙሺ።

30 የይሁዳ ልጆች በፊቴ ክፉን ነገር ሠርተዋል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ያረክሱትም ዘንድ ስሜ በተጠራበት ቤት ርኵሰታቸውን አኑረዋል።

31 እኔም ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ያለችውን የቶፌትን መስገጃዎች ሠረተዋል።

32 ስለዚህ፥ እነሆ፥ ስፍራ ከማጣት የተነሣ በቶፌት ይቀበራሉና የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።

33 የዚህም ሕዝብ ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚያስፈራራቸውም የለም።

34 ምድሪቱም ባድማ ትሆናለችና ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም አደባባይ የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ አጠፋለሁ።